Imaginary stories based on oral history

ክፍል ፩

የማርገጃ ሰፈር ትዝታዬ

       የእህል ውሀ ነገር መሀል ሸገር ላይ ሲጥደኝ የሚከራይ ቤት  ፍለጋ እግሬ የረገጠው የጨርቆስን ምድር ነበር፡፡ ያውም የጨርቆስ እንብርት በሆነችው ማርገጃ መንደር ላይ፡፡ 

  ጨርቆስ ውስጥ እንኳን ሰው ቤቶችም እርስ በእርስ ተደጋግፈው እንደሚኖሩ የሚገለጥልህ ማርገጃ ላይ ስትደርስ ነው፡፡ ማርገጃ ይሄን ስያሜዋን ያገኘችው ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ወደ ቂርቆስ ቤ/ክርስቲያን ለቀብር የሚመጣ ለቀስተኛ የሟችን ግብዓተ መሬት ከማስፈፀሙ በፊት እዚች መንደር ላይ አረፍ ብሎ የሙሾ ስርዓት ማከናወኛ በመሆኗ የተነሳ እንደነበር ነዋሪዎቿ ይናገራሉ፡፡

   እድል ገጥሞህ በማርገጃ መንደር የሚከራይ ቤት አግኝተህ ከገባህ ስለቤት እቃ መጨነቅ አከተመለት፡፡ እንኳን ፍራሽ ትራስ ለመዘርጋት በምትጠብ ቤት ውስጥ ንብረት መያዝ የግድ ካለህም ማርገጃዬ ምን አጥታ!!!

     ከቁም ሳጥን እስከ ሬሳ ሳጥን ድረስ ጠጋግና እና ቀባብታ በርካሽ ብር እነሆ በረከት ትልሃለች፡፡ ማብሰል ሲያምርህም የጎረቤት ቡታጋዝ ግድግዳህን ተደግፎ ታገኛለህ፡፡ ካንተ የሚጠበቀው የነዳጅ ወጪዋን ሸፍነህ መለኮስ ብቻ ነው፡፡

 

     ማርገጃ ላይ ቆዝሞ ለመዋል ትልቅ ጥንካሬ ይጠይቃል ፡፡ ምንም እንኳን ስያሜዋን በሙሾ ማውረጃነት ሰበብ ብታገኘውም ዛሬ ላይ ዋነኛ መተዳደሪያዋ የነዋሪዎቿ ክሽን ቀልዶችና ፍልቅልቅ ፈገግታዋ ነው፡፡ የወር ደሞዝ ቢርቅብሀ እንኳን  እንደ ጤና ቢሮ የ24 ሰዓት የምርመራ  ሪፖርት በጉጉት አትጠብቀውም ፡፡ ባይኖርህም ስቀህ ታድራለህና፡፡

     የዚህ መንደር ነዋሪዎች ቀልድ አዋቂነት በእድሜ የምትገድበው አይደለም፤ ከልጅ እስከ አዋቂው በንግግሩ መሃል ጣል የሚያደርግብህ ነገር አያጣም ፡፡ ለዚህ ማሳያ እንዲሆንህ ስለ አከራዬ (እማማ ዬሺ) ትንሽ ልበልህማ ፡፡

       እማማ ዬሺ ማርገጃ ላይ ተወልደው ወደ እርጅናው እየተንደረደሩ ያሉ እናት ናቸው ፡፡ ስለ አስተዳደጋቸው ከተነሳ “ እድሜ ለማርገጃ እትብቴ እንኳን ሲቀበር በማርሽ ባንድ ታጅቦ ነው!” ብለው ያፈዙሃል ፤ ስለ ልጆቻቸው ከጠየክም “የእኔ ልጆች እጅግ ጨዋ ከመሆናቸው የተነሳ ቁምሳጥን እንኳን ሲከፍቱ አንኳክተው ነው” ሲሉ ትሰማለህ፡፡

       አንድ ቀን አምስት ሊትር የሚረጋውን ዘይት ከሸማቾች ገዝተው ሲመለሱ አግኝቼ  “ እማማ ይሄን ዘይት ባይጠቀሙ ጥሩ ነው ሽባ ነው የሚያደርጎት” ስላቸው ምን ቢሉኝ ጥሩ ነው “ አረ ተወኝ ልጄ…. ሽባ የሚያደርገውስ ሰልፉ!”

 

       

          //ይቀጥላል // 

Imaginary stories based on oral history

©2018 BY AFETARIK.