Imaginary stories based on oral history

ክፍል ፬

ዳትሰን ሠፈር እና ጥበበኞቿ

Heading 1

    

 

      በአንድ ወቅት እንደክፉ ሚስት ጠዋትና ማታ የምትነዘንዘኝን የጥበብ ዛር ለማስታገስ ስል ልፅፍ ተነሳሳሁ፡፡ ከንሮዬ ላይ ሸራርፌ ባገኘዋት ትርፍ ሰዓት አንዲት ለአቅመ ተውኔት የምትበቃ ስክሪፕት ፅፌ እንደጨረስኩ ትገመገምልኝ ዘንድ ከቀናኝ አዋቂ ካልሆንም ታዋቂ አርቲስት ለማግኘት መዳከር ጀመርኩ ። መቼም እዚች ሀገር ላይ የታዋቂ አርቲስት አድራሻ ከመፈለግ ታዋቂ መሆን የሚቀል ይመስለኛል ።ከቀናት ሙከራ በኋላ የአንድ ዝነኛን ልብ አራርቶልኝ በተለምዶ ዳትሰን ሰፈር በምትባል አካባቢ እንድንገናኝ ቀጠሮ ያዘልኝ፡፡ በንጋታው ከበሬው በላይ የተገለገልኩበትን ቆዳ ጃኬቴን  በዴኦዶራንት አጥኜ ወደ ቀጠሮዬ ቦታ መጣደፍ ጀመርኩ፡፡ በዚህ መልኩ ነበር እኔና ዳትሰን  የመጀመሪያውን ትውውቅ ያደረግነው፡፡

      ዳትሰን ከፒያሳ ግርጌ ላይ ተቆርቁራ በሰሜን ሆቴል፣ በዮሀንስ፣ በሾላ ገበያና ገዳም ሰፈር መሃል ሳንዱች ሆና ኑሮዋን በመግፋት ላይ የምትገኝ መንደር ነች፡፡ አሁን ላይ የምትጠራበትን ስያሜ ያገኘችው በ1970 ዓ/ም አካባቢ  እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዛ ወቅት ወ/ሮ አለሚቱ ይማም የተባሉ የተሁለደሬ ባር ባለቤት በዘመኑ ዘናጭ የነበረችውን ዳትሰን መኪና በአስራ ስድስት ሺህ ብር እጃቸው ያስገባሉ ፡፡ እሳቸውን ተከትሎም ሌሎች አራት ሴቶች ቀልባቸው ያረፈባትን ዳትሰን መኪና ወደ ሀገር አስገብተው በየግሮሠሪዎቻቸው በራፍ ላይ መደዳውን በሰልፍ ማቆም ይጀምራሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ቀደም ሲል ቤርሙዳ እየተባለች ትጠራ የነበረችው መንደር ቀስ በቀስ የመኪኖቹን ስያሜ የራሷ መጠሪያ እንዳደረገችው ይታመናል፡፡

     ጥበብ ከቀበሌ ኪነት አንስታ ዓለም ሲኒማ ላይ ያስቀመጠችው ዝነኛው አርቲስት በምልክት በነገረኝ አቅጣጫ መሠረት አንድ ሁለት ኩርባዎችን ታጥፌ ወደ ቀጠሮዬ ግቢ ደርሻለሁ፡፡ የግቢውን በር አልፌ ወደ ውስጥ መግባት ስጀምር በቴሌቪዥን መስኮት  ብቻ የማውቃቸው  ትላልቅ አርቲስቶች ትናንሽ ፍራሽ ላይ በዮጋ ስልት ዱቅ ብለዋል፡፡ ዙሪያቸውን በጫት ገራባና በአድናቂዎቻቸው ተከበው  የአረብ ሀገሩን ሳክስፎን (ሺሻ) በላይ በላይ ይሉታል፡፡ ይሔን ባየው ቅጽበት የዳትሰንዬ ቀን ላይ በዝምታ መዋጥ በጉያዋ መሽገው የሚውሉ አርቲስቶቻችን  ለተመስጦ እንዲረዳቸው መሆኑ ተገለጠልኝ፡፡በቤቱ ውስጥ ከሳክስፎኑ ከሚወጣ ድምፅ ውጪ ኮሽታ የለም፡፡ አንዱ ይፅፋል፣ አንዱ ይገጥማል ሌላው በምርቃና መሀል የመጣለትን ዜማ በሆዱ እያዜመ ለመሸምደድ ይሞክራል….በዚህ መልኩ ተከሽነው በሚወጡ የኪነ ጥበብ ውጤቶች አድማጭና ተመልካቹ ሳይቅም እየመረቀነ ሳይጠጣ ይሰክራል፡፡

 

     ከአርቲስቱ ጋር የነበረኝን ዘለግ ያለ ቆይታ ፈፃፅሜ የያዝኳትን ስክሪፕት አስገምግሜ (አስቅሜ)  ግርማ ሞገሳሙን ግቢ ለቅቄ ስወጣ ቀን ላይ “ነብስ ይማር” ለማለት ያዳዳኝ የዳትሰን ጭርታ መልኩን ቀይሯል፡፡ የመሸታ ቤቶቿ በራፎች ተከፋፍተው በብልጭልጭ መብራቶችና በቄጤማ አሸብርቃ እንቁጣጣሽ መስላለች፡፡ አዝማሪ ቤቶቿ የከበሮአቸውን ምት ከማሲንቆው ድምፅ ጋር እያስማሙ የደንበኞቻቸውን ጅምር ስንኞች በዜማ ያሽሞነሙኑታል፤ ጭፈራ ቤቶቿን ከሀገርም ከውጪውም እየቀላቀሉ አስረሽ ምቺውን ተያይዘውታል፤ ድምፃዊያኖቿ ከምርቃና ላይ ተነስቶ እንደመጣ በሚያስጠጣ ቅላፄ “አልመሸም ገና ነው ዳመና ነው” እያሉ ከዜማ ጋር ትግል ጀምረዋል፡፡

 

እኔ ቢመሽብኝም ዳትሰን ገና እየነጋላት ነው……

 

                                                    ………..እንቀጥላለን……..

©2018 BY AFETARIK.